ውፍረትና የጤና መዘዙ

ውፍረትና የጤና መዘዙ

(መጋቢት 04/2005, በመታሰቢያ ካሣዬ, (አዲሰ አበባ))–ወደ ሰውነታችን ውስጥ የሚገቡ ምግቦች የሃይል ምንጭ ለመሆን ወደ ጉሉኮስነት መቀየር ይኖርባቸዋል፡፡ ሰውነታችን በራሱ ተፈጥሮአዊ ዘዴ ምግቦችን ወደ ጉሉኮስነት የመቀየሩን ተግባር ያከናውናል፡፡ በምግብ መልክ ወደ ሰውነታችን ውስጥ የገባው ሁሉ የሃይል ምንጭ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ሰውነታችን ከሚፈልገው የሃይል መጠን በላይ የሆነው ምግብ በሰውነታችን ውስጥ በስብ መልክ ይከማቻል፡፡ይህ የስብ ክምችትም በተለያዩ የሰውነታችን ክፍል ውስጥ በሥጋ ላይ ተለጥፎ ይገኛል፡፡ ሰውነታችን የምግብ እጥረት ሲያጋጥመው እነዚህን የስብ ክምችቶች እያቃጠለ ለሃይል ምንጭነት ይጠቀምባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምግብን ባገኙት ሰዓት ያለገደብ የሚመገቡ ሰዎች ግን የስብ ክምችታቸውን ከዕለት ወደ ዕለት እያሳደጉት ይሄዳሉ፡፡ አመጋገባቸው ጨምሮ አካላዊ  እንቅስቃሴ የማያደርጉ ከሆነ ደግሞ የስብ ክምችቱ መጠን በከፍተኛ መጠን ይጨምራል፡፡

በአጠቃላይ ውፍረት ስንል መነሻው ሰውነት ለሃይል አቅርቦት ከሚፈልገው መጠን በላይ ምግብ መውሰድ ወይንም አመጋገቡ ከወትሮው ያልተለየ ሆኖ ከአካላዊ እንቅስቃሴ መገደብ ነው፡፡ ወይም ውፍረት የሚፈጠረው የሚወሰድ የሃይል ምንጭ ከሚያስፈልገው የሃይል አቅርቦት ሲበልጥ ነው፡፡

ለተለያዩ ከሰውነት ክብደት መጨመር ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች መጋለጥ ዋንኛ ምክንያት የሆነው የክብደት ግዝፈት ዓይነት (BMI) የሚባል ሲሆን ይህም ከ30 እና ከዚያ በላይ በሚሆንበት ጊዜ ለበሽታ የመጋለጡን እድል ሰፊ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ በሽታዎች ሊያጋልጥ በሚችል ውፍረት መጠን ውስጥ እንዳሉ ለማወቅ የወገብንና የዳሌን ዙሪያ ልክ በሴንቲ ሜትር ለክቶ ለሁለት ማካፈል ነው፡፡ በዚህ ውጤት መሠረት ልኬቱ በወንዶች ከአንድ ቁጥር ከበለጠ በሴቶች ደግሞ ከ0.9 ከበለጠ እነዚህ ሰዎች ሆዳቸው አካባቢ ከፍተኛ የሆነና ለተለያዩ ህመሞች የሚያጋልጥ የስብ ክምችት አላቸው፡፡

ከውፍረት ጋር በተያያዘ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል በተለይ ለከፍተኛ የደም ግፊትና የስኳር ሕመም ችግሮች የሚያጋልጠው ይኸው በሆድ አካባቢ የሚከማቸው የስብ መጠን ነው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ለሚከማቸው ስብ የተለያዩ ምክያቶች ቢኖሩም ዋንኞቹ ግን የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የአመጋገብ ባህላችን
አብዛኛዎቻችን የምግብ ምርጫችን ወደ እንስሣት ተዋፅኦና ጣፋጭ ምግቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ሥጋ፣ እንቁላል፣ ቅቤና ወተት በምግባችን ውስጥ ካላካተትን የጋበዝንም የተጋበዝንም የማይመስለንና ለምግብ መመገቢያ የተወሰነ ሰዓትና ጊዜ የሌለን ከመሆኑም በተጨማሪ ምግብን የምንመገበው ስለተራብን ብቻ ሣይሆን ስለአገኘንም መሆኑ ሠውነታችን ከሚያስፈልገው የሃይል ምንጭ በላይ ምግብ እንዲወሰድና ከአስፈላጊው በላይ የሆነው በስብ መልክ እንዲከማች ምክንያት ይሆነዋል፡፡

2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አለማድረግ ወደ ሰውነታችን ውስጥ የገባና ከአስፈላጊ በላይ የሆነው ምግብ በተለያዩ መንገዶች መቃጠልና ከሰውነታችን ውስጥ መወገድ ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ ግን በስብ መልክ ያከማቻል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አካላዊ ብቃት እንቅስቃሴ ስንልም በተደራጀ መልኩ በጄምናዚየምና መሰል ሥፍራዎች ላይ ብቻ የሚደረገውን ሳይሆን ሰው በዕለት ተዕለት ተግባሩ ራሱን በማንቀሳቀስ፣ የእግር ጉዞ በማድረግ እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ምግቡ እንዲቃጠል ማድረግ ይኖርበታል፡፡

በእርግጥ ያለንበት ዘመን ቴክኖሎጂው የተስፋፋበት መንገድን በመኪና ደረጃና በሊፍት የምናሳጥርበት ሁኔታ የተመቻቸበት ቢሆንም ማንኛውም ሰው በተለይ ደግሞ የውፍረት ችግር ያለበት ሰው ራሱን በእነዚህ ነገሮች ውስጥ በማንቀሳቀስ ደረጃዎችን በእግሩ በመውጣት፣ በአንቀሳቃሽ የቢሮ ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ራሱን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሊያግዝ ይችላል፡፡

3. በዘር የሚከሰት የውፍረት ችግር
የውፍረት ችግር በዘር የመተላለፍ ዕድል አለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለከፍተኛ ክብደት የሚያጋልጡ የዘር ዝንፈቶች አሉባቸው፡፡ ይህ የዘር ዝንፈትም ሰውነት ምግብን ለሃይል ምንጭነት በማዋል ከማቃጠል ይልቅ እንዲከማችና ስብ እንዲፈጥር በማድረግ ውፍረትን ያባብሳል፡፡

ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች
ከፍተኛ የደም ግፊት
በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ የኮሎስትሮል ክምችት እንዲኖር በማድረግ የደም ግፊት ንረትን ይፈጥራል፡፡

የስኳር ህመም
ሰውነት በኢንሱሊን እንዳይታዘዝ በማድረግ ለስኳር ህመም ያጋልጣል

የልብ ህመም ችግር
የልብ ጡንቻ ዝለት እና የልብ ድካም በማስከተል በልብ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ይፈጠራል

ካንሰር
በጣም ወፍራም የሆኑ ሰዎች በተለያዩ ካንሰር ዓይነቶች የመያዝና ዕድሜያቸውን የማሳጠራቸው ዕድል ከቀጫጭኖቹ የሰፋ ነው፡፡ ውፍረት ከሚያስከትላቸው የካንሰር ዓይነቶች መካከል የትልቁ አንጀትና ፕሮስቴት፣ በሴቶች ላይ ደግሞ የሀሞት ከረጢት ካንሰር፣ የጡት የማህፀንና የኦቫሪካንሰሮች ዋንኞቹ ናቸው፡፡

ስትሮክ
አንጐል ደም እንዳይደርሰው በማድረግ ለድንገተኛ የህሊና መሳት ችግር ሊያጋልጥ ይችላል

የአተነፋፈስ ችግር
በደረት ላይ በሚከማቸው ስብ አማካኝነት በደረት አካባቢ ከፍተኛ ውፍረት ስለሚኖር የደረት አጥንቶች ይህንን ክብደት በተፈለገው መጠን ለማንቀሳቀስ ይቸገራሉ፡፡ ይህም እንደልብ መተንፈስ አለመቻልናንና ቶሎ መድከምን ያስከትላሉ፡፡

የአጥንት መገጣጠሚያ ህመሞች
ከፍተኛ የሰውነት ክብደት በዋንኛነት የሚሸከሙት የአጥንት መገጣጠሚያዎች ናቸው፡ በመሆኑም በእነዚህ የአካል ክፍሎች ላይ ህመም የሚከሰት ሲሆን ሪህም በውፍረት አማካኝነት ከሚመጡ የጤና ችግሮች መካከል ተጠቃሹ ነው፡

ውፍረትን እንዴት መከላከል/ማስወገድ ይቻላል?
ውፍረት ሳይከሰት መከላከሉ እጅግ የበዛ ጠቀሜታ እንዳለው አይካድም፡፡ የአመጋገብ ሥርዓታችንን በማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግና ህይወትን በሥርዓት በመምራት ውፍረትን ከመምጣቱ በፊት ልንከላከለው እንችላለን፡፡ ውፍረቱ ከተከሰተ በኋላስ ተያያዥ ችግሮቹን ከማስከተሉ አስቀድሞ እንዴት ማስወገድ እንችላለን?

አመጋገብን ማስተካከል
ከፍተኛ የካሎሪ ምንጭ የሆኑ ምግቦችን በእጅጉ መቀነስ እነዚህም እንደ ቅባት፣ ጣፋጭ ምግቦችና ስብ የበዛባቸው ጮማ ምግቦች ናቸው፡፡ በእነዚህ ምትክ አነስተኛ የካርቦሃይድሬት ይዘት ያላቸውን ምግቦች ማለትም ጥራጥሬዎችና ልዩ ልዩ የእህል ዘሮች መመገብ፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ የበለፀጉ ምግቦችን በዕለት የምግብ ዝርዝራችን ውስጥ ማካተት፤ አንድ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያለው ሰው በቀን 1000 ካሎሪ የሚደርስ መጠን ያለው ካሎሪ ብቻ በመውሰድ ቢገደብ ከፍተኛ የክብደት መጠን መቀነስ ይኖረዋል፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
ክብደትን ለመቀነስ በአካል ውስጥ የተከማቸው ስብ መቃጠል ይኖርበታል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ክብደትን ከመቀነስ ባሻገር ለሰውነት ጤና መሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በተለይም እንደስኳርና የደም ግፊት ላሉ በሽታዎች አጋዥ የህክምና ስልት ነው፡፡

መድሃኒት
አመጋገባቸውን አስተካክለው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴንም ተግባራዊ አድርገው ክብደታቸው ሊቀንስላቸው ያልቻለ ሰዎች፤ የምግብ ፍላጐትን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን በአማራጭነት ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ መድሀኒቶች መካከል ፌንፊሉራሚን፣ ሲቡትራሚን እና ፊንቴራሚን የተባሉት መድሃኒቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ቀዶ ጥገና
ከተገቢው የሰውነት ክብደት በላይ 45 ኪሎ ትርፍ ያላቸው ሰዎች ክብደታቸውን በአመጋገብ፣ በአካል እንቅስቃሴና፣ በመድሃኒት ጭምር ታግዘው መቀነስ ካልቻሉ የመጨረሻው አማራጫቸው የቀዶ ጥገና  ህክምና ማድረግ ነው፡፡
ይህ የቀዶ ጥገና አይነትም የጨጓራን የምግብ አቀባበል አቅም ማሳነስ ሲሆን ይህም ችግሩ ያለበት ሰው አነስተኛ ምግብ ብቻ እንዲጠቀም በማድረግ የክብደት መቀነሱን ያፋጥናል፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

About The Author

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

X
Welcome to ESCF Website
Welcome to ESCF Website
WooChatIcon